Sep 16, 2016

ፎረም 65፦ አክቲቪስቶችና ፓለቲከኞቻችን - ከአቶ ሽመልስ ወርቅነህ

ሕዝባዊ ንቅናቄው ከተቀጣጠለ አነሆ አመት አየተጠጋ ነው።  በተለይም በጉልህ የኦሮሞ ሞቭመንት አና የአማራው ሞቭመንት በመባል የሚታወቁት ሁለቱ  ንቅናቄዎች  ሚሊዮኖችን ያሳተፈ በመሆኑ ሕዝባዊነቱ ሌላ ማረጋገጫ አያስፈልገውም።  ወያኔ ኢሕአዴግ በሕዝባዊ ንቅናቄና በፖለቲካ ስልጣን ጥያቄ መካከል ያለው ልዩነትና ዝምድና ከባህርዩ የተነሳ ሊገነዘብ ባለመቻሉ ሕዝባዊ ንቅናቄውን የጥቂት ፖለቲከኞች ወይም ጸረ ሰላም ሃይሎች አድርጎ በመቁጠር በተለመደ ጥቂቶችን የማጥፋት የጉልበት ስልቱ ሕዝባዊ ንቅናቄውንም ለማዳፈን ደፋ ቀና እያለ ይገኛል። ይህም እኩይ ተግባሩ በየቀኑ ከሕዝብ አየነጠለው እነሆ አሁን ጠመንጃውን የሚያዙ ጥቂቶች አየተንገዋለሉ ይገኛሉ። 
በቲዎሪም ሆነ በተግባር ለወያኔ ኢሕአዴግ የሚቀርበው የሌኒን የአብዮት ቲዎሪ አብዮትን ለማምጣት የሚያስፈልጉ ሁኔታዎች ብሎ የገለጻቸው እንደ ቀድሞ መግዛት አለመቻልና ተገዥውም አነደቀድሞው ለመገዛት ፈቃደኛ አለመሆን የወቅቱ የሃገራችን ሁኔታ መገለጫ ነው።  ሌሎች ሁኔታዎች ማለትም በተለይ ህወሃት ኢሕአዴግ በራሱ ሊያመጣ የሚችለው ስር ነቀል ለውጥ አስከሌለ ድረስ አብዮቱ መምጣቱ አይቀርም የሚመጣው አብዮት ደግሞ የአረብ አብዮት ቢጫ፣ ብርቱካን፣ ሰማያዊ አብዮት አያለ ስራቱ የሕዝብን አንቅስቃሴ መገለጫዎችን የሚቀልድባቸው አይነቶች ሳይሆን ኢትዮጵያዊ አብዮት እንዲሆን የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች ከወዲሁ ሊያደርጉዋቸው የሚገቡ ተግባራት አንዳሉ ሁኔታዎች አያስገደዱ ናቸው ።
ብዙዎቻችን አንደምንረዳው ሕዝባዊ እንቅስቃሴው ሞልቶ የገነፈለ የወያኔ ኢሕአዴግ አገዛዝ ብሶት የወለደው ንቅናቄ ነው።  የኦሮሞውም ሆነ የአማራው ንቅናቄ በሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ስርዓቱ ከሚያደርሰው በደል ፈጽሞ የተለየ በመሆኑ ሳይሆን በፖለቲካ ብልጣብልጥነት በተለይ ህወሃት በማናለብኝነት በሕዝብ ትግል የተገኙ ድሎችን ሁሉ በችሮታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠ አንደ ፈጣሪ አንተ ያመጣህልን አየተባለ አንዲኖር በዚህም ጥቂቶች ከአጋሮቻቸው ጋር በምግባረ ብልሹነት በሙስና በአጠቃላይም የመላው ሃገሪቱን  ፖለቲካ ኢኮኖሚ ጠቅልሎ በመያዝ የሚታየው ለከት የለሽ ዝርፊያ አልበቃ ብሎ ከማንኛውም አካባቢ በከፋ በሁለቱ ሕዝቦች ላይ አየፈጸመ ያለው ግድያ፣ አፈና እስርና እንግልት ያስመረረው መሆኑ ነው።  የንቅናቄው ጫሪ ምክንያትም ይህ ነው።  የአዺስ አበባ ማስተር ፕላንም ሆኑ የወልቃይት ጉዳይ ጫሪ ምክንያቶች አንጂ ዋነኛ ጉዳዮች አይደሉም።  ዛሬ ወያኔ ኢሕአዴግ እነዚህን ጉዳዮች በመፍታት ንቅናቀውን ለማፈን ደፋ ቀና እያለ ቢሆንም ሕዝባዊ አመጹ ከእንግዲህ የማይመለስበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
የሕዝብ አንቅስቃሴ ይሄን አይነቱን ከፍተኛ ህይወትን ጭምር ለመስዋአትነት የሚዳርግ የሕዝብ ቁጣ ለዘመናት የተንከባለለ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍትህ፣ የነጻነትና የእኩልነት የማንነትና የዜግነት ጥያቄዎች ያለመመለስ ምክንያቶች ናቸው።  ምንም እንኳን የሃገራችን ችግሮች ሁሉ ወያኔ ኢሕአዴግ የፈጠራቸው ናቸው ባይባልም ህወሃት/ኢሕአዴግ የነበሩትን ችግሮች መፍታት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ችግሮቹን ለመፍታት የተነሳበት መነሻ ሃስቡና በተለይ ህወሃት ከነበረው አገራዊና በብሄር ጥያቄ ስም የተከተለው የጎጠኝነት ፖለቲካ በጎ ሰራሁ የሚላቸውን ነገሮች ሁሉ በበጎነት ሊወስድ የሚችል ትውልድ መፍጠር አለመቻሉ በተለይ በኦሮሞውም ሆነ በአማራው ንቅናቄ በፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የማይመለስ ትውልድ እያበበ መምጣቱን የምንመለከተው።
ከላይ ለመግለጽ አንደሞከርኩት ይህ ንቅናቄ በራሱ ብቻ የመጣ ነው ማለትም አይደለም ።  ባለፉት ፪፭ አመታት አየወደቁና አይተነሱ አስካሁን እዚህ የደረሱት የፖለቲካ ድርጅቶች ምንም እንኳን የራሳቸው ድክመቶች ቢኖራቸውም የሚያነሷቸው የሕዝብ ጥያቄዎችና ማታገያ መፈክሮች የሕዝቡን ንቃተ ህሊና በማዳበርና የትግል ተነሳሽነትን በመፍጠር ያበረከቱትን ድርሽ መካድ አይቻለም። የሚፈለገውን ያህል ጠንክረው ለእንዲህ አይነቱ እንቅስቃሴ የፖለቲካ አመራር ለመስጠት የሚያስችል ብቃት ባያገኙም ቢያንስ በሃገር ቤት በሰላማዊ ትግል ሲታገሉ የነበሩ ድርጅቶች ሕዝቡን በመቀስቀስና በማስተባበር አንዲሁም በሁለገብ አንታገላለን ያሉትም ቢያንስ ለመስዋአትነት ያላቸውን ቁርጠኝነት የወጣቱን ተነሳሽነት አጎልብቶታል። በዚህ መልኩ በኦሮሚያ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ፣ በአማራው መኢአድ፡ አንድነትና ኢዴፓ ይጠቀሳሉ። በትጥቅ ትግል እንሳተፋለን ያሉት አርበኞች ግንቦት 7 እና ኦነግ በትጥቅ ትግል ያሳዩት ውጤት ባይኖርም ወደ መጨረሽው ሕዝባዊ አመጽን አንደዋነኛ የትግል ስልት አድርገው መንቀሳቀሳቸው የወጣቱን የትግል ፍላጎት አነሳስቷል።
እንግዲህ ይህ ከሆነ ዛሬ የሚታየው ሕዝባዊ ንቅናቄ አቅጣጫና አመራር በማን አጅ ነው ያለው? ወዴትስ ነው የሚወስደን? የሚለው ጥያቄ መመለስ ያለበትና የሕዝባዊ ንቅናቄው ፍሬያማ እንዲሆን በግልጽና በድፍረት መነካት ያለበት ጥያቄ ይሆናል ።  ሕዝባዊ ንቅናቄውን በማስተባበርና በመምራት ረገድ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች አየተናበቡ ነው ወይ የሚለው ወቅታዊ ጥያቄ መነሳት አለበት። በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለያዩ አክቲቪስቶች የሚሰጡዋቸውን መግለጫዎች ለምንከታተል ሰዎች አልፎ አልፎ ግራ የሚያጋቡ ነገሮችም ይስተዋላሉ።  አንዳንዶቻችን በአሁኑ ወቅት ወያኔ አሕአዴግን ከመጣል ባሽገር ይህን መሰል ጥያቀዎችን ማቅረብ በራሱ የፖለቲካ አቋም መመዘኛም አያደረግነው ነው።  ይህ ደግሞ መሰረታዊ ጥያቄና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ ታሪክ የብዙሃንን ህይወት የቀጠፉ የለውጥ ሂደቶች የታየ መሰረታዊ ጉድለቶቻችን ናቸው።  
አጼውን መጣል አንጂ ስለሚከተለው ዝግጅት አልነበረም፤ ደርግን መጣል አንጂ ስለሚከተለው ማንም አላሰበውም። አሁንም አንዳንዶች ወያኔን መጣል አንጂ የሚከተለውን ማሰቡ አስፈላጊ አለመሆኑን በማስፈራራት ጭምር (“ይህን ካነሳህ ወያኔ ነህ” አይነት ፖለቲካ ሲያራምዱ ይታያሉ)። በየቀኑ በመላ ሃገሪቱ በአምባገነኑ ስርዓት የሚፈሰው ደም ክቡርነትን የምናረጋግጠውና የትግሉንም ሕዝባዊነት የሚወስነው በሚሞቱት ወገኖቻችን ቁጠር መብዛትና ማነስ ሳይሆን የያንዳንዱን መስዋአት ከፋይ ዜጋ ህይወት በከንቱ አለማለፉን ስናረጋግጥ ነው።  በሞት ከሆነ አስከዛሬ በሃገራችን ለውጥን ለማምጣት የተከፈለውን ህይወት መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል። በተለይም በደርግ ዘመን ያለቀን ትውልድና አስካሁንም በዚህ ስርዓት ያለቀውን ትውልድ ማስታወስ ያስፈልጋል ።  የሚከፈለው መስዋአትነት ወደ ትክክለኛ ግብ ሊያደርስ የሚችል መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው።
ዛሬ በአማራውም ሆነ በኦሮሞያ በዚህ ጨፍጫፊ ስርዓት የሚሞቱት ህጻናትና ወጣቶች ክቡር ህይወትን ክቡርነት የሚያረጋግጥ ሃላፊነትን የሚወስድ ሃይል መኖር አንዳለበት ግልጽ ነው።  ምንም እንኳን እስካሁን ሕዝባዊ እንቅሳሴውን መርቶ ወደተፈለገው አቅጣጫ ለማድረስ የተዘጋጀ ሃይል ስብስብ ባይኖርም እስከምናውቀው ሁለት የንቅናቄ ሃይሎች ማለትም ኦሮሞ ሞቭመንት አና አምራ ሞቭመንት የሚሉ የአክቲቪስቶች ስብስብ ዋነኛውን ቦታ ይዞ አንደሚገኝ አጠያያቂ አይደለም ።  እነዚህም በኦሮሞውም ሆነ በአማራ ውስጥ የነበሩ ባለፉት አመታት የነበሩ የተበታተኑ አክቲቪስቶች በሕዝባዊ እንቅስቃሴው ገፊነት የተፈጠሩ ለመሆናቸው ጥያቄ የለውም ።  በዳበረ ፖለቲካ ውስጥ አክቲቪስቶች በስልጣን ላይ ያለን መንግስት ወይም ስርዓት ያወጣቸው ፖሊሲዎችና ህጎች አንዲለወጡ የሚፈልጉ ለለውጡም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ ዜጎች ናችው።  በፖለቲካ ሳይንስ ተንታኞች ሶስት አይነት አክቲቪስቶች አሉ።
  1. Past oriented or Reactionary activism የዚህ አይነቱ አክቲቪዝም  ጉልበተኞችና ስልጣን ላላቸው በመወገን ያለው አንዲቀጥል በደካሞች ላይ የገዥዎች ጭቆና አንዲቀጥል የሚያበረታቱ ወይም የሚረዱ ወይም  ያለፈ ታሪክ ላይ ብቻ ያተኮረ የፖለቲካ አስተሳሰብና የለውጥ ሃሳብ የሚያራምዱ ናቸው።  በሃገራችን ለምሳሌ ባይበሉም  ሆዳሞች የምንላቸው አይነቶች
  2. Present oriented Activism የዚህ አይነቱ አክቲቪስም የፖሊሲ ለውጥን ግቡ ያደረገ በሌላ በኩል በስርዓቱ ውስጥ መሻሻል አለባቸው ብለው የሚያምኑባቸው ጉዳዮች ላይ አጥብቀው የሚሟገቱ በሌላ በኩል ጥገናዊ ለውጥን አንደመፍት ሄ የሚያቀርቡ በሃገራችን ጎልቶ የማይታይና በሁለቱም በኩል የሚመጡ
  3. Future oriented Activism የዚህ አይነቱ አክቲቪስም የፖሊሲ ለውጥ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰባዊ ግንኙነት ለውጥ፣ የስርዓት ለውጥ እንዲኖር የሚታገሉ ናቸው።  በሃገራችን  አሁን ባለው ፖለቲካ ይሄ ክፍል ይበዛል፤ በተለይ በዲያስፖራው ጎልተው የሚታዩ።
እዚህ ላይ በፖለቲከኞችና በአክቲቪስቶች መካከል ያለውን ግንኙነትና ልዩነት ማየቱ ለበለጠ ግንዛቤ ይረዳል። ፖለቲከኞች እንደየሃገሩ ተጨባጭ ሁኔታ በሃይልም ይሁን በምርጫ የመንግስትን ስልጣን ይዘው የተወሰነ አይዲዮሎጂን በመከተል ይሁን በተግባር ለመተርጎም ወይም እፈጽማለሁ ብለው ቃል የገቡትን ሃሳብ በተግባር ለማዋል የሚፈልጉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች (የፖለቲካ ድርጅት) እና ፖለቲከኞች የሚፈልጉትን ለማግኘት አስተሳሰብን በመቀየር በመግባባት በመስማማት  compromiose በማድረግ ወይም አንደ ህወሃት/ኢሕአዴግ ስብስቦች በጉልበት የሚፈልጉትን ያስፈጽማሉ።
አክቲቭስቶች ግን አላማቸው ስልጣን ለመያዝ ሳይሆን የህብረተሰቡ ህይወት ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አስተሳሰቦች ፖሊሲዎች አንዲቀረጹና የቡድን ወይም የተወሰነ ህብረተሰብ ክፍል ብሶትና ጥያቄ በመቀስቀስ ለአፈጻጸሙ የተለያዩ የሰላማዊ ትግል ስልቶችን በመጠቅም ለተግባራዊነቱ ይታገላሉ። ለዚህም ነው አንዳንድ ጊዜ  “Poletician get activists to do their dirty jobs” የሚባለው።
ሰሞኑን በኦ.ኢም.ኤን ሬዲዮና በፌስ ቡክ ቀርበው የነበሩ ሁለት አክቲቪስቶች ውስጥ በኦሮሞ ፕሮተስት ትልቁን ሚና አየተጫወተ ያለው ጀዋር አሁን የሚታየውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አስመልክቶ እንቅስቃሴው ወዴት አንደሚያመራ ለቀረበለት ጥያቄ የስጠው መልስ ይህን በሚገባ የሚያሳይ ለመሆኑ “ ወዴት እንደሚያመራ የሚመልሱት የፖለቲካ ድርጅቶች መሆናቸውንና አማራውም ሆነ ኦሮሞው  በመጀመሪያ በራሱ ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች መፍታት አንዳለበት” የሚያመለክተው አነጋገሩ የአክቲቪስትነትን ተልዕኮ በሚገባ ያመለክታል።  ለዚህም ነው አንዳንድ ወሳኝ የሆኑ ከንቅናቀው ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ገና ባየር ላይ ያሉ መሆናቸውን የምንረዳው። በእርግጥም ዛሬ በሃገራችን ያለውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ አመራር ለመስጠት እየሞከረ ያለው አክቲቪስቱ አንደሆነ ለመረዳት አያስቸግርም።
ሃገራችን የአክቲቪስቶች ሃብታም ናት፤ የፖለቲከኞች ደሃ መሆናችን ግን መጠራጠር አይቻልም ።  ድህነትና ባለጠግነት ባለህ መጠን ብቻ የሚለካ ሳይሆን ኖሮህም መኖርን ሳታቅበት የምትኖር ከሆንክ ከደሃው አትሻልም።
አንዳንድ ወገኖች አሁንም የሃገራችን  ሁኔታ ይህን ጥያቄ ማስተናገድ የለበትም ሁሉም በአንድ ላይ ሆኖ ወያኔን የማስወገድ ተልዕኮ አስካለው ድረስ በፈለገው አቅጣጫ መሄድ ይችላል የሚለው የያንዳንዱን ህይወት ከፋይ ዜጋ ክቡር ህይወት ግምት ውስጥ የማያስገባ በተወሰኑ የስርዓት ለውጥ ፈላጊ አክቲቪስቶችና አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲንጸባረቅ መታየቱ ነው።  ይህን ጥያቄ መመለስ አለመቻሉ ነው የፖለቲካ ድርጅቶቻችን በጋራ አምባገነኑን ስርዓት አንዳይታገሉ ህብረተስባችንም በስልጣን ላይ ካለው አምባገነን መንግስት የተሻለ የሕዝብን አንድነት ፍቅር መተሳሰብና ልዩነቶቹን አቻችሎ ሊመራው የሚችል በየፊናው  በመግለጫ የሚያለቅስለት ሳይሆን በተግባር የተሳሰረ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ፣ አማራ አትዮጵያዊ፣ ትግሬ አትዮጵያዊ፣ ሶማሌ ኢትዮጵያዊ ቀለም ያለው የፖለቲካ ሃይል የሚናፍቀውና ይህን አስከሚያገኝ በጥርጣሬ ህይወት የሚያደርገው ብልጭ ድርግም ንቅናቄ ምክኛቱ ይኽው ነው።  ለዚህም ሃገራችን በቁጠር ብዙ ፖለቲከኞች ቢኖራትም የፖለቲከኞች ደሃ ነን የሚያሰኘው።  
ፓለቲከኛነት የምታምንበትን አላማ ወይም ለሕዝብ የገባሀውን ቃል (በጠመንጃ ሳይሆን) ከሕዝብ በሚሰጥህ ስልጣን ተጠቅመህ በመንግስታዊ ተቋም አምካይነት የማስፈጸም አቅም መገንባት ነው። ዛሬ ያሉን የፖለቲካ ድርጅቶች አላማቸውን ለሕዝብ አቅርበው ሕዝብ ሊዳኛቸው የሚችልበት ስርዓት ስለሌለን ትግሉ ያንን ስርዓት ለማምጣት አንደሆነ አይካድም። ያንን ስርዓት ደግሞ ለማምጣት ወደፊት ሊፈጽሟቸው የተዘጋጁባቸው ተግባሮችን ያሰፈሩት በፕሮግራሞቻቸው ነው።  አንዳንድ የማይናቅ   ድጋፍ  ያላቸው  የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ ፕሮግራም የሌላቸውና በንቅናቄ ደረጃ የሚጠሩ መሆናቸው ግልጽ ነው።  እንግዲህ እዚህ ላይ ነው የዛሬ ሃያ አመት ወይም ሰላሳ አመት የያዙትን የፖለቲካ አቋምና አቋማቸውን ሊፈጥር የቻለውን የህብረተሰቡን ፖለቲካዊ  ማህበራዊና አኮኖሚያዊ አደረጃጀት ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ የጋራ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል የጋራ መታገያ አጀንዳና ራዕይ አስከሌለ የመተባበርና የትግል አጋርነት አንደናፈቀን ያለው።
አክቲቨስቶቻችን የያዙት የአማራና የኦሮሞ ወይም የሌላው ንቅናቄ መተባበር ውጠቱ ስርዓቱን ለመጣል ከሚደረግ የታክቲክ ጥያቄ የዘለለ አስካሁን በፖለቲካ ድርጅቶች ሰፊ የልዩነት ፕሮግራም ላይ የጠበበ በጋራ ሊያሰራ የሚችል ሃስብ መምጣት የነበረበት ከፖለቲካ ድርጅቶቹ ነው።  ጃዋር እንዳለውም ሃላፊነቱ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ከሆነ ለዚህ ሕዝባዊ ንቅናቄ የጋራ አመራር ሊሰጥ የሚችል የፖለቲካ ሃይል በዚህ ጊዜ ውስጥ መታየት ነበረበት ።  አንዳንዶች ወስጥ ለውስጥ አየሰራን ነው ቢሉም ግንቦት ሰባትና ኦ.ዲ.ኤፍ የጋራ የትግል ህብረት መመስረታቸውን መግለጻቸው የአማራውንና የኦሮሞውን ትግል የማቀናጀት እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል አይደለም። በነዚህ ድርጅቶችና በሕዝባዊ ንቅናቀዎቹ መካከል ያለው መተሳሰር ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ቢያስቸግርም የሃገራችን የፖለቲካ ችግር በሁለቱ ድርጅቶች መስማማት ይቋጫል ማለት አንዳልሆነ ግልጽ ነው።  
ጅምራቸው ግን አጅግ ሊበረታታና የጎደላቸውን ለማሙዋላት ከሚደረግ ጥረት እነሱንም ለማፍረስ የምንጥር ከሆነ አላማችን የሕዝብን ችግር የመፍታት ጥያቄ ሳይሆን ችግር ፈጣሪዎች መሆናችንን የሚያመለክት ነው። ማንኛውም የመተባበር ጥያቄ ፍሬያማነት ወደፊት የምንመሰርታት ሃገር የማነች የሚለውን ጥያቄ በሚገባ ማሳየት መቻሉ ወሳኝነት አለው።  የቁጥር ትልቅነትና ትንሽነት በማህበራዊ አስተዋጿችን ላይና በጥቅም ተካፋይነት ላይ የሚኖረንን የተጠቃሚነት ወይም የተሳትፎ መጠንን የሚያመለክት አንጂ የሰው ልጅነትና እንደሰው በሚያስፈልጉ ነጻነቶች ላይ ገደብ ሊኖረው እንደማይችል እሙን ነው። የአማራውና የኦሮሞው ቁጥር መብዛት መታየት ያለበትም ከዚያው አንጻር ነው።  አምባገነኑ ስርዓት በሁሉም ህብረተሰብ ላይ የሚያደርሰው በደል መገለጫ በግለሰቦች ላይ የሚያደርሰው በደል ነው።  የወደፊቱ ኢትዮጵያም የማንኛውንም ግለሰብ ህልውናና መብት ማስከበር ቀዳሚ ተግባር መሆኑን መተማመን ካለ ሕዝብ ወደ ትግሉ ይበልጥ ይቀላቀላል።
አንዳንድ አክቲቪስቶቻችን አስካሁን ይጓዙ የነበረበትን በአስገዳጅ ሁኔታዎችም ጭምር የቡድን ብቻ አስተሳሰብ ወጣ እያሉና ወደ አጠቃላይ ህብረተሰብ ችግር አፈታት ውስጥ እየገቡ ያሉ ቢሆንም በፖለቲካ ድርጅቶች ሊረዱና ሊታገዙ እስካልቻሉ ድረስ ትግሉን ውስብስብ ያደርገዋል።  አክቲቭስቶች ቀጥታ ለፖለቲካ ስልጣን የሚታገሉ ባይሆንም ወደፊት የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ የሚያስችል ፍላጎት ወይም እድል የላቸውም ማለት አይደለም ።  በዚህም ሁኔታ በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ወይም ታዋቂነት ከፍ ከፍ ለማድረግ አይጥሩም ማለት አይደለም ።  በተለይ እንደኛ ሃገር ጠንካራ መሪዎችና ባብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መሪዎች ጎልተው በማይወጡበት ሁኔታ ውስጥ ወይም አክቲቪስቱና ፖለቲከኛው በተደበላለቀበት ሁኔታ ውስጥ ወይም ሚናቸው ተለይቶ በማይታይበት ሁኔታ ውስጥ እያንዳንዱ አክቲቪስት የሚሰጠው አመራር ሁነታዎችን ከቁጥጥር ውጭ እንዳያደርግ መጠንቀቅ አስፈላጊ ይሆናል።
በመሰረቱ በሃገሩ ጉዳይ ጊዜውን ጉልበቱን አቅሙን ገንዘቡን ሁሉ መስዋአት በማድረግ በሚችለው መስክ ሁሉ ድርሻውን የሚያበረክት ሁሉ አክቲቪስት ነው።  የተወሰኑ የሚዲያ ያገኙ ብቻ አክቲቪስት ናቸው ማለትም አይደለም። አልፎ አልፎ (እንደማአረግ አየሰጠን ነው ያለነው) ሚዲያ ላይ የቀረበ ሁሉ የሚያቀርበው ሃሳብ የሃገርን ችግር መፍጤ ይሰጣል ማለትም አይደለም።  ለዚህ ነው የፖለቲካ ድርጅቶች የተለያዩ አክቲቪስቶችን ሃሳብ አመለካከት አሰባሳቢ የሆነ የፖለቲካ ማታገያና መታገያ ሃስብ ዪዘው መቅረብ የሚገባቸው።
በፖለቲካ ውስጥ ዋስትና የለም፣ ፓለቲካ ዳይናሚክ ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው።  የፖለቲካ ዳይናሚዝም ግን በየሳምንት ሃሳብን መቁዋጠሪያ በሌለው መገለባበጥ የሚገለጽም አይደለም ።  ቢያንስ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጸና አቋም ሊታይ ይገባል።  የሰው መገደልን ዛሬ በምክንያት አስደግፈህ ማስተባበልና ነገ ደግሞ በምክንያት አስደግፈህ መቃውም የፖለቲካ አቋም ዳይናሚዝም አይደለም።  ይህ መሰረታዊ ጤናማ አዕምሮ ከመጀመሪያው ሊያወግዘው የሚገባ አቋም ነው።  የፖለቲካ  ዳይናሚዝም በሕዝቦች አስተሳሰብና አመለካከት ላይ ተመስርቶ የሚመጣ የግለሰብ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለውጥም ነው።  ዛሬ የአማራና የኦሮሞ ሞቭመንት በሕዝብ አመለካከት ላይ የተፈጠረ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው።  ከአክቲቪስችንም ከዚህ ዳይናሚዝም ጋር አብሮ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የሚጠበቅ ነው።  የአስተሳሰብ ለውጡን ደግሞ በስርዓትና ወጥነት ባለው አክሄድ ወደግቡ አንዲያመራ ግቡን ማሳየት  ፡ የፖለቲካ ድርጅቶችና ፖለቲከኖች ተግባር ነው።
በአቶ ሽመልስ ወርቅነህ
Share:

ተልዕኳችን | Our Mission

“65 ፐርሰንት” ትርጉም? የኢትዮጵያ ህዝብ 65 በመቶው እድሜያቸው ከ24 አመት በታች ነው። ተልዕኳችን ለመጪው ትውልድ የመግባባትን ፓለቲካ በአርአያነት ማውረስ ነው። ግባችን ለፓለቲካዊ እርቅና መግባባት መሟገትና ፋና ወጊ መሆን ነው።

What is “65 percent”? 65% of Ethiopia’s population is under 24 years old. Our mission is to model a culture of political concensus for the 65%. Our goal is to advocate for, and initiate reconciliation and consensus among Ethiopians.

Post Archive